ዋናዋ ጠላቴ ያመጣኍት ሚስቴ

ደራሲ - አሚጎ ዞሮመጣ


ሁለት ወጣቶች በፖለቲካ ምክንያት ተሰደው ካገር ይወጡና ከብዙ ችግር በኍላ በግራቸው ተጉዘው ሱዳን ይገባሉ - ከዚያም እንደማይሆን የለምና ለአራት አመታት ስቃይን በቁና ሲሰፍሩ ቆይተው

ወንድየው በተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ኮሚሽን እርዳታ ካናዳ ሄዶ እንዲኖር ይፈቀድለታል - እዚያም ሶስት አመት እንደቆየ ዜግነቱን ያገኝና ሌት ተቀን ሰርቶ ገንዘብ አጠራቅሞ ሱዳን ስደተኛ ጣቢያ

የምትኖረውን ፍቅረኛውን በሕጋዊ መንገድ ያሰመጣትና እንደ ባልና ሚስት ሆነው መኖር ይጀምራሉ - ይህ በዚህ እንዳለ በመሀል ሁልት ልጆች ይወለዱና ቀስ በቀስ ፍቅሩ ሲቀዘቅዝ ኑሮ ካቅም በላይ ሲሆን

መቸም ያለ ነገር ነውና በሆነ ባልሆነው መጨቃጨቅ ይጀመራል - በዚህ ሁኔታ ለጥቂት አመታት አብረው ይቆዩና ወደመጨረሻ ነገሩ ሲከር ሚስት ባልዋን ሳያስበው ተከሰዋለች - ከዚያም ጉዳዩ

በጠበቆቻቸው አማካኝነት ክሱ ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ከቀረበ በኍላ ዳኛው በሕጉ መሰረት ፍርዳቸውን ይሰጣሉ - በመጨርሻም ሚስት የምትኖርበት ቤት ሲመርቅላት - ባል ግን እጅና እግሩን ይዞ

እንዲወጣ ይደረጋል - ይህን አስመልክቶ ካገራቸው ውጪ በትዳር የሚኖሩ ሰዎች ለምንና እንዴት እንደማይግባቡ እንዲሁም የውጪው አለም የህጎች ደምብ በሚመለከት ከሞላ ጎደል ላንባቢያን ትንሽ

እውቀት ይሰጣል ብዬ ስለገመትኩ በግጥም መልክ የሚቀጥለውን ድርሰት አቅርቤአለሁ -

ባል


እኔ ድሮ ሳቅሽ የድሀ ልጅ ነበርሽ

አሁን አዚህ መጥተሽ አጉል ተንቀባረርሽ

ወይ አምላኬ ስትይ የምትበይው አተሽ

የሱዳን በረሀ ማዲያታም አድርጎሽ

እራሴን ጎድቼ ከዚህ ጉድ ባወጣሽ

ለሰሚው ግራ ነው እንደህ መጥገብሽ


ሚስት


አንተ ማን ሆነህ ነው እንዲህ የምትለው

ኑሯችን እንደሆን የሚመሳሰል ነው

አባትህም ቢሆን የጠገበ ህብታም

ሀብቱን ያካበተው ስርቶ አይመስለኝም

እቅጩን ብነግርህ ኍላ እንዳትቀየም

እንዲህ የምትንቀኝ የምታዋርደኝ

ትንሽ የቀውስ ዘር ያለብህ መሰለኝ


ባል


እንዴት እንዲህ ብለሽ ስሜን ታጠፊያለሽ

የቀውስ ዘር ያለሽ አንቺ ትመስያለሽ

የጠጉርሽ አስራር የቅንድብሽ መቆም

የምትለብሽው ልብስ ማጠርና መርዘም

መቀወስሽ እንኳን አያጠራጥርም


ሚስት


ስለኔ አለባበስ የጠጉር አሰራር ምንም አያገባህ

አሁን የምኖረው አገር ቤት መሰለህ

ለማደርገው ነገር ለምን ተጨነቅህ

አፍህን ካልዘጋህ እተኛልሀለሁ ከገዛ ጕደኛህ

የሚበጅ መሰለኝ ብትቀመጥ አርፈህ


ባል


አሁን ገና ገባኝ ውስጠ ሚስጥርሽ

ከጕደኞቼ አንዱ ትንሽ ቢቀምስሽ

ባይንሽ ታይዋለሽ ሞት ሲያፘርጥሽ

ውርደቴን ታቅፌ እንዴት እኖራለሁ

አንችንም ገድዬ እኔም እሞታለሁ

ደሞም ከፈለኩኝ ከፎቅ ላይ ዘልዬ እከሰከሳለሁ


ሚስት


እንኳን መግደል ቀርቶ ጫፌን አትነካኝም

ከፎቅም ላይ ብትዘል እኔ አያገባኝም

መፍጨርጨር ነው እንጂ ምንም አትፈይድም

ሰው ታሰለቻለህ ነገር ስተደጋግም

ተጠንቀቅ- ፖሊስ ከጠራሁኝ አስሮ ያሶጣሀል

የማይሆን ከሆነ በሰላም ብትሔድ ላንተ ይበጅሀል

ባል


ልጆቼን በትኜ ወዴት እሄዳለሁ

ተቻችለን ብኖር ይሻላል እላለሁ

አለዚያ ግን ጦሱ ለሁላችንም ነው

ፖሊስ ብትጠሪ ማነው የሚፈራው


ሚስት


የማይበርድ ከሆነ ይህ አጉል ትእቢትህ

ፖሊስ ልጠራ ነው እዚህ ቁጭ ብለህ

ከንግዲህ በኍላ ከሱ ተነጋገር ከኔ ምንም የለህ


ፖሊስ


በሩን ኳኳ አድርጎ እቤት ይገባና

ችግሩ ምንድነው እስኪ ወደዚህ ና

አንተ ነህ ጎረምሳው የምትረብሸው

ከሆነስ ሆነና የትነው የምትስራው

መጠጥ ነው ድራግ እንዲህ ያደርገው

አንድ ሀጥያት ስርቶ ነው አይኑ የፈጠጠው

ለምንድነው አንተ የምትረብሽው?


ባል


እረ እኔ ጌታዬ ምንም አረበሽኩም

መጠጥም ድራግም ወስጄ አላቅም

ግን አንዳንድ ጊዜ ቢራ እጠጣለሁ

ጠንብዤ ጠጥቼ ማንንም አልነካሁ

እንዲያው ዝም ብላ ነው እሳ የጠራችሁ

ስራየም እንደሆን ዲሽ ወሽር ነበርኩኝ

ዛሬ ገና ድንገት ሳላቅ ተባረርኩኝ


ፖሊስ


እሳ ሥራ የላት አንተ ሥራ የለህ

በተለይ አንተማ እንዴት ትኖራለህ

ያልታወቀ ገቢ አይቀርም ሣይኖርህ

በል አሁን ተነሳ ወደ ጣቢያ እንሂድ

ላደረከው ጥፋት ዳኛው እስከሚፈርድ

አንቺ ደሞ ስሚ የምነግርሽን

ቃሉን ተቀብለን ነገ በጠዋቱ እንለቀዋለን

እስከዚያ ድረስ ግን ዝጊ በርሽን

ደግሞ ካስቸገረ ደግመሽ ደውይልን

እንደ ፋሲካ በግ እንጎትተዋለን በግር ብረት አስረን


ሚስት


አመስግናለሁ ለትብብራችሁ

እዝች ከደረሰ እጠራችኻለሁ

ልጆች ማሳደጊያ ገንዘብ ስለሌለኝ

በየወሩ እንዲከፍል ግዳጅ አስገቡልኝ

በሉ በተረፈ በሰላም ዋሉልኝ


ባል ፍርድ ቤት ቀረበ


ዳኛ


ጉዳዩ ምንድነው እስኪ ዘርዝርልኝ

የተጠራው ፖሊስ ሚስትህን በቡጢ መተሀታል አለኝ

በል ምንም ሳትዋሽ ሚስጥሩን ንገረኝ


ባል


እንኳን መምታት ቀርቶ መጥፎ አልተናገርኳት

አሁን ምን ያደርጋል ይኸ ሁሉ ውሸት

እኔ አላቅበትም እንዲህ ያለ ሙግት

ጠበቃ ይሰጠኝ በተቻለ ፍጥነት


ዳኛ


ጠበቃ መጠየቅ ሕጋዊ መብትህ ነው

ነገር ግን አንተ ነህ ገንዘብ የምትከፍለው


ባል


ከየት አምጥቼ ነው ገንዘብ የምከፍለው

የወር ገቢ የለኝ ወይ ስራ ምሰራው

ብድር እንኳ ሚሰጥ አላውቅም አንድም ሰው

መፍትሄ ፈልጉ ሥልጣኑ የርሶ ነው


ዳኛ


መንግስት ይሰጥሀል የግል ጠበቃ

ሌላ ርዳታ የለም ከዚህ በላይ በቃ

ቀስ በቀስ ከገቢህ እከፍላለሁ ብለህ

ሕጋዊ ዶኩመንት መፈረም አለብህ


ባል


እሺ እፈርማለሁ ምንም ችግር የለ

መክፈል እችላለሁ ገንዘብ በጄ ካለ

እድሜዎን ያርዝመው እንደ ማቱሳላ

አይረዳኝም ነበር ዳኛው ቢሆን ሌላ


ባል የሕግ ጠበቃ አገኘ


ጠበቃ


አሁን አነበብኩት የክሱን እሪፖርት

ነገሩ ከባድ ነው እኔ እንዳየሁት

ጊዜ ያስፈልጋል በጥልቀት ለማጥናት

ከሳምንት በኍላ ስልክ እደውላለሁ ጠብቀኝ በትግስት


ከሳምንት በኍላባል


የመጀመሪያው ቀን ሹልክ ብለው ሄዱ በደንብ ሳንተያይ

እርሶን የመስለኛል በየመንገዱ ላይ ቦርሳ የያዘ ሳይ

በነገራችን ላይ እምን አደረሱት ያንን የኔን ጉዳይ

ጠበቃ


ምንም ችግር የለ ባንተዋወቅ

ጉዳይህ እንደሆን ይሰራል በሐቅ

እዚያው ሄጄ ነበር በቀጠሮ ቀን

እኔም እረዳቴም አንድ ላይ ሆነን

እዳኛው ፊት ቀርበን ስንከራከር

የሚስትህ ጠበቃ ትንሽ አለው ግር

የኍላ የኍላ ድሉ የኛ እንደሆን አትጠራጠር

ነገም ይሁን ዛሬ ይዘህልኝ ብቅ በል ሁለት ሺ ብር

ባልስለ ገንዘብ ጉዳይ ችግር አለብኝ

በየወሩ ልሰጥ ፈርሜአለሁኝ

የማይሆን ከሆነ እንዳሻሁ ያርጉኝ


ጠበቃ


ያለ ገንዘብማ ማን ይሰራልሀል

ነገሩ በንጥልጥል ባለበት ይቆማል

አንተን አስኮንና ሚስትህ ከረታችህ

ያልታሰበ ችግር ባንተ ቢደርስብህ

እኔ ጋ እንዳትመጣ ይረዳኛል ብለህ


ባል


የተከራከሩት አንድ ቀን ብቻ ነው

ሁለት ሺ ብሩ ከየት የመጣ ነው

በሰአት ሀምሳ ብር እንኳ ቢከፈሉ

እንዴት አርባ ሰአት ሰራሁኝ ይላሉ

ነገሩ ግራ ነው ለሚሰማው ሁሉ


ጠበቃ


ብዙ ወጪ አለ አንተ የማታቀው

መዘርዘር አልችልም የግል ጉዳይ ነው

ላንተ መከራከር ምንም ጥቅም የለው

ሌላ ጠበቃ አቁም አቤት በል ለዳኛው


ባል --- ለዳኛው


ጌታዬ ነገሩ ተጓተተብኝ

የሰጡኝ ጠበቃ ገንዘብ አምጣ አለኝ

አስቀድሜ ለርሶ ነግሬዎ ነበር ቤሳ እንደሌለኝ

የሚቻል ከሆነ ሀቀኛ ጠበቃ ይሰይሙልኝ


ዳኛ


በትላልትናው ቀን ፍርዱ ተፈርዶብህ ነገሩ እኮ ሞቷል

እኔ እንደሰማሁት ላንተም ሁኔታውን ጠበቃህ ነግሮሀል

የፍርዱን ውሳኔ አነባለሁ ብትል

ይኸው ግልባጬ ውሰድና አብተልትል


የመጨረሻ ፍርድ


ለልጆችህ እናት ግማሹ ከገቢህ ተቆርጦ እንዲሰጣት

እሱዋ ካልፈቀደች ከቤትዋ አካባቢ ድርሽ እንዳትላት

ልጆችህን ግና በሳምንት አንድ ቀን ትችላለህ ማየት

ሥራ እንደምትሰራም ማስረጃ ስላለን በጃችን እግዚቢት

ሁለት ሺ ብሩን ለዚያ ለጠበቃህ ክፈለው በፍጥነት

አለበለዚያ ግን ትዛዝ እሰጣለሁ እንድትገባ እስር ቤት

የዛሬው ፍርዳችን የመጨረሽያ ነው ይግባኝ የሌለበት

ከንግዲህ በኻላ መልካም ቀን ያርግልህ በል በደህና ሰንብት=-=-=-=-=-=-=-=-= ተፈጠመ =-=-=-=-=-=-=-=-=-=-


Nov 29, 2010

Chapter-2 ..... Next
© 2016 Ethcartoons.net